የሀገራዊ ራዕይ አልባነት ጉዞ እስከ መቼ? (ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ)

ሀገራዊ ራዕይ የረዥም ጊዜ ኾኖ የሚቀመጠው በማዕቀፍ ነው፡፡

ሀገራዊ ራዕይ የረዥም ጊዜ ኾኖ የሚቀመጠው በማዕቀፍ ነው፡፡ ለዛ ማዕቀፍ የሚረዱ ግቦች፣ ዓላማዎችና ተልዕኮዎች በአንጻሩ ይኖራሉ፡፡ የአንድ ሀገር ራዕይ ዕምነት – ሀገራዊ ማዕቀፍ ነው፡፡ የሀገራዊ ማዕቀፍ ምሰሶዎች በአንጻሩ ሀገራዊ ርዕይ በነጠላ፤ ሀገራዊ ግብ ለራዕዩ፤ ሀገራዊ ዓላማዎች ለግቡና ለርዕዩ፤ ሀገራዊ ተልዕኮዎች ለሀገራዊ ግብና ርዕይ መሣካት ይኖራል፡፡

ዓለም ከሥልጣን ፖለቲካ ወደ ፖለቲካ ተሻግሮ፤ ስለታሪክ ከመነታረክ ወጥቶ ታሪክ ስለመስራት በሚታገልበት፤ ከጥቃቅንና አነስተኛ ሀሳቦች ወጥቶ እጅግ ወደ ላቀና ውሰብስብ ሀሳብ በገባበት፤ ከÕዳ ፖለቲካ ወደ አደባባይ ፖለቲካ፣ ከድንበር ተሻግሮ በዓለም አቀፋዊነት በሚተጋበት – እኛ ከከባቢያዊነት ወደ መንደርተኝነት ስንገሰግስ፤ ዓለም ወደ ፊት ቀን ከለሊት ሲተጋ እኛ ወደ ኃላ እያሰብን ሴራ ስንጎነጉን፤ ዓለም በነገ ማዕቀፍ ሲተጋ – እኛ በትላንት ማዕቀፍ ለመኖር ስንተጋ፤ ፖለቲካችን እንደህጻን ልጅ በትናንሽ ነገሮች እየረካ፤ ዓለም ከመሬት ፍትጊያ ወደ ስፔስ ፍትጊያ ሲገባ የኛ ነገር – ነገር መብላት ብቻ ቢኾን ለምን ብሎ መጠየቅ ዜጋዊ ግዴታ ኾነና ጥያቄ አነሣን፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ‘የሀገሪቱ አጠቃላይ ርዕይ “ከ2012 – 2015 ባለው ጊዜ ውስጥ በሕዝብ ተሳትፎና በሕዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና መልካም አስተዳደር የሰፈነባት፣ ማኅበራዊ ፍትህ የነገሰባት፣ ከድህነት ተላቃ መካከለኛ ገቢ ያላት ኢትዮጵያን ዕውን ማድረግ፤” የሚል ርዕይ እንዳለ ይገለጻል፡፡

‘መካከለኛ ገቢ’ የሚለው ግብ እንጂ ርዕይ ፈጽሞ ሊኾን እንደማይችል ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ያውም ከግብም ቢኾን የአጭር ጊዜ ግብ ምክንያቱም ግብ በራሱ የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ተብሎ ስለሚከፈል፡፡ እንደሀገር እኛ ኢትዮጵያውያን ለምንድነው መካከለኛ ገቢ ያላት ሀገር የምንፈልገው? የት ለመድረስ? ለምን? የሚለው ወደ ርዕይ የሚያመላክተን ሲኾን ምን ሀገራዊ ማዕቀፍ ስላለን ነው? የሚለው ደግሞ ዐቢይ የሀገራዊነታችን ማሳያ ሀገራዊ ማዕቀፍ ይኾናል፡፡

ሀገራዊ ርዕያችን ምንድነው? እዛ ለመድረስስ ምን ምን ማድረግ አለብን? በባለቤትነት ስሜት እንዴት ልንይዘው እንችላለን? ሀገራዊ ማዕቀፋችንን መሠረት ያደረገው እምነታችን፣ ዕውቀታችንና ተግባራችንስ ምንድነው? ማህበራዊ ፍልስፍናችንስ ምንድነው?

የፖሊሲ ዓላማዎችና ግቦች የሀገር ዓላማና ግቦች ናቸው ማለት አይደለም፡፡ የአንድ ነጠላ ሀገራዊ ዕቅድ ዓላማ ማለት ጠቅላላ ሀገራዊ ዓላማ ማለት አይደለም፡፡ ዕቅዱ የሀገሪቱ ባጠቃላይ የረዥም ጊዜ ዓላማና ግብን ለማሳካት የሚረዳ አንድ መሣሪያ  መኾኑ ላይ ከፍተኛ ጽንሰ ሀሳባዊ ክፍተት ከመኖሩም ባሻገር ነጠላ ፖሊሲዎችና ሀገራዊ ፕሮግራሞች ላይ የሚቀመጡ ዓላማና ግቦችን – የሀገር ዓላማና ግብ አድርጎ የመውሰድ ከፍተኛ ጽንሰ ሀሳባዊ ክፍተት አለ፡፡

ለአብነት፡ ‘የመጀመሪያው የአምስት አመት የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ’ በሚል በተደጋጋሚ የሚገለጸውን የወሰድን እንደኾነ እንደሀገር ያልተመለሰው ዐቢዩ ጥያቄ ዕቅዱ ላይ ከተቀመጡ ዓላማዎችና ግቦች ባሻገር ለምንድነው ሀገራችን ይህ ዕቅድና ትራንስፎርሜሽን ያስፈለጋት? የት ለመድረስ? መቼ? በምን? ለምን? ስለምን? የሚሉ ዐበይት ሀገራዊና ሕዝባዊ ትርጉም ያላቸው ሀገራዊና ሕዝባዊ ጥያቄዎችን  – ትርጉም ባለው መልኩ ምላሽ አይሰጥም፡፡

ራሱን ዕቅዱን እንˆ ብናይ “ዕቅዱ ከምንጊዜውም የላቀ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ማኅበራዊ ልማትና መልካም አስተዳደር የሚመዘገብበት፣ ከሚመዘገበው ውጤትም ሕዝቡ ፍትሃዊ በኾነ መልኩ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበትና የዜጎችን ማኅበራዊ ዋስትና ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ይታመናል፡፡” በማለት ድህነትን ለማስወገድ፣ ለብልጽግና፣ ዲሞክራሲ ለማዳበር፣ ሥራ አጥነትን ለመቀነስ፣ ጤናን ለማስፋፋት፣ መሰረተ ልማትን ለሁሉም ለማድረስ – – – የሚሉ ጥቅል ሀሳቦችን ያነሣል እንጂ ትርጉም ባለው መልኩ ሀገራዊ ርዕይ፣ ሀገራዊ ግብ፣ ሀገራዊ ዓላማን ከዕቅዱ ግብ፣ ዓላማና ተልዕኮ ለይቶ አያስቀምጥም፡፡

   የዕቅዱ ግብ፣ ዓላማና ተልዕኮ ማለት የሀገር ግብ፣ ዓላማና ተልዕኮ ማለት አይደለም፡፡ ዕቅዱ ራሱ የሀገራችን ኹለንተናዊ እንቅስቃሴ አንድ አካል ብቻ ተደርጎ ነው መወሰድ ያለበት፡፡ ሀገራችን ሳትኾን የዕቅዱ አካል – ዕቅዱ ነው የሀገራችን ኹለንተናዊ እንቅስቃሴ አንድ አካል መኾን ያለበት – ሊኾንም የሚችለው፡፡

በፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች ላይ የፖሊሲና ፕሮግራም ዓላማ፣ ግብና ተልዕኮ መገለጽ ሀገራዊ ርዕይ፣ ሀገራዊ ግብ፣ ሀገራዊ ዓላማ አለን አያስብልም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ጥቅል ከመኾናቸውም ባሻገር እንˆንስ እንደመንግሥት እንደግለሰብ እንˆ መሠረታዊ ጽንሰ ሀሳባዊ ጉድለት ያለባቸው በመኾኑ ነው፡፡

ይህም ክፍተት በዋናነት ለምን? በምን? ስለምን? የሚል ሕዝባዊና ሀገራዊ ትርጉም ያለው ጥያቄን – ትርጉም ባለው መልኩ የማይመልስ መኾኑ ነው፡፡ ዲሞክራሲ፣ ፍትህ፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት፣ ተደራሽነት፣ ሰላም፣ ብልጽግና፣ መልካም አስተዳዳር – – – ለምን? የት ለመድረስ?

ሀገራዊ ርዕይና ግብን በሚመለከት ለአብነት ቻይና፡-

“The firmly believe that the goal of bringing about a moderately prosperous society in all respects can be achieved by 2021, when the CPC celebrates its centenary; the goal of building china in to a modern socialist country that is prosperous, strong, democratic, culturally advanced and harmonious can be achieved by 2049, when the people’s republic of china marks its centenary; and the Dream of the Rejuvenation of the Chinese nation will then be realized.” የደመቁና የተሰመረባቸውን ቃላት ለምን? እንዴት? በምን? መቼ? በማን? የሚሉ ሕዝባዊና ሀገራዊ ጥያቄዎችን ትርጉም ባለው መንገድ ያስቀመጠ፣ ተያያዥና ተመጋጋቢ ተግባራትን በግልጽ ያሰፈረ፣ በፕሮፕጋንዳ ቃላት ያልተሸፈነ ግልጽ ሀሳብ የያዘ፣ በአሳማኝ ጭብጦች የተደገፈ እን£ን ለዜጎ„ – ለኛ ቻይናን ለመረዳትና ለመገንዘብ ያስቻለ እንደኾነ ግልጽ ይመስለኛል፡፡

እኛ ርዕይ ብለን ያስቀመጥነውን ስንመለከት – ምን ያክል በአስተሳሰብ ኃላ እንደቀረንና በሀሳብ ድሃ እንደኾንን አመላካች ነው፡፡ በሌላ በኩል ከፕሮፕጋንዳ ይልቅ ግልጽ፣ ተያያዥና ኹሉን የሚያቅፍ ብሎም ትውልድ ተሻጋሪ የኾነ ጽንሰ ሀሳብ የያዘ ነው፡፡ የኛ ግን ከጽንሰ ሀሳባዊ ትስስር ይልቅ ፕሮፕጋንዳዊ ቃላት የሚበዙበት እን£ን ትውልድ የሚሻገር ሊኾን ርዕይና ግብ የተምታታብን ስለመኾናችን ብዙ ጥናትና ምርምር አይጠይቅም፡፡

ከዚህ ባሻገር የሀገራችን ብሔራዊ ጣቢያ በየዕለቱ የሚለው፤ መሪዎች በየዕለቱ የሚያስተጋቡት፤ ምሁራን ዘወትር የሚጽፉበት-የሚመራመሩበት፤ ኹለንተናዊ ልዩነቶችን መሸከም የሚችል፤ እንደሀገር ሕዝብ እንደሕዝብ ያለ ልዩነት በባለቤትነት ስሜት ይዞ የሚያነሣው የጋራ የኾነ ትርጉም ያለው ሀሳብን ከጽንሰ ሀሳባዊ ጥልቅ ሀገራዊና ሕዝባዊ ዕሳቤ ጋር የያዘ ርዕይ የለንም፡፡ ለነገሩ ርዕይ ሳይኖር እንዴት ይገለጻል?

ነገር ግን እንደሀገር ጠቅለል ያለ ርዕይ ባይኖርም /በድጋሚ ርዕይ ተብሎ የተገለጸው ግብ – ከግብም ቢኾን የአጭር ጊዜ ግብ እንጂ ርዕይ ፈጽሞ ሊኾን ስለማይችል/ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እና የተለያዩ የመንግሥት አካላት ርዕይ፣ ተልዕኮ በማለት የሚገልጹትና የለጠፉትን ስንመለከት፡-

 1. ጽንሰ ሀሳባዊ መዘበራረቅ፤
 • በርካታ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ርዕይ ብለው የሚያስቀምጡት ሥራቸውን ነው፡፡
 • ለአብነት፡-

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት

 ርዕይ፡ “ጠ/ሚኒስትሩና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ህገ መንግሥታዊ ተልዕˆቸውን በብቃት ተወጥተው ማየት፤”

ይህ ማለት ጠ/ሚኒስትሩም ኾነ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ኃላፊነታቸው፣ ግዴታቸውና ሥራቸው በራሱ ርዕያቸው መኾኑ ነው፡፡ እንዴት ነው ሥራቸው ርዕይ ሊኾን የሚችለው?

 • እንዲህ ዓይነት ክፍተቶች በበርካታ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና የመንግሥት አካላት የሚታይ ነው፡፡
 • ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲህ ከኾነ – እንዴት ነው እሱ የሚሰበስባቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የጠራ፣ ግልጽና ተመጋጋቢ የኾነ ርዕይ ማዘጋጀት የሚችሉት? የሀገራችን ሥርዓት ራስ እንዲህ ከኾነ ከሌላው ምን ይጠበቃል? ይህ ጽህፈት ቤት እንዲህ ከኾነ እንደሀገር ርዕይ እንደሌለን – ከዚህ በላይ ምን ማስረጃ ይኖር ይኾን?
 1. የይዘት አቀማመጥ ጥራት መÕደል
 • በርካታ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና የተለያዩ የመንግሥት አካላት ርዕይና ግብን ቀላቅለው – ርዕይን ባለማስቀመጥ ግባቸውን ርዕይ ብለው ይገልጻሉ፡፡
 • በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ የጊዜ ገደብ ተቀምጦ የሚገልጹ አካላት በሙሉ እንዲህ ያለ ክፍተት የሚታይባቸው ናቸው፡፡

– የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት

ርዕይ፡– “በ2015 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ የሕዝብ አመኔታ የተቸረው ፍርድ ቤት ኾኖ ማየት፤”

– የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ትራንስፖርት ሚኒስቴር

ርዕይ፡ “በ2017 ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ትራንስፖርት አገልግሎት ተደራሽ ሆኖ ማየት፤”

 • (በጣም የሚያሳዝነው ‘ርዕይ’ ተብሎ ራሱ የተገለጸውን እንዳለ ብንቀበል ከነ ክፍተቱ – የሀገሪቱ አጠቃላይ ‘ርዕይ’ – &በ2012 – 2015 ዓ.ም – መካከለኛ- ገቢ& ሲል ይህ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ግን ‘በ2017 ዓ.ም’ ብሎ የራሱን ‘ርዕይ’ ያስቀምጣል፡፡ አንድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ካጠቃላይ ሀገሪቱ ርዕይ በላይ ጊዜ ካስቀመጠ ይህ በራሱ ትርጉም ያለው፣ ጥልቅ፣ ሰፊ፣ ተናባቢ፣ ወጥና ተመጋጋቢ የኾነ ሀገራዊ ርዕይና ግብ እንደሌለ ተጨባጭ ማስረጃ ሲኾን በሌላ በኩል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ካጠቃላይ ሀገራዊ ርዕይ በመነሣት የድርሻቸውን መውሰድ እንዳለባቸው ግድ የሚለውን መርሕ በእጅጉ የሳተ ኾኖ እናገኘዋለን፡፡)

በመሠረተ ሀሳብ ደረጃ የጊዜ ገደብ ያለው ነገር ግብ እንጂ ርዕይ ሊኾን አይችልም፡፡ ርዕይ ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ – ትውልድ ተሻጋሪና ረቂቅ የዘውትር ሥራና የማይቀያየር መኾኑን መዘንጋት የማያሻ ይኾናል፡፡

እነዚህ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ከጠቀሱት ዓመተ ምህረት በ‰ላ ማሳካት ሚፈልጉት ምንድነው? ሥራ ያቆማሉ ማለት ነው? ለምንድነው በጠቀሱት ዓመተ ምህረት ላይ ማሳካት ሚፈልጉትን የጠቀሱት? የት ለመድረስ? ለምን?

 1. የአድማስ ጥበት፤
 • ርዕይ ማለት እጅግ በጣም የረዥም ጊዜና ዘመን የማይጥለው ዘመንን መዋጀትና ከዘመን ጋር መራመድ የሚችል ትላንትን ከዛሬ፤ ዛሬን ከነገ ጋር ማገናኘት የሚችል የዕሳቤ ውጤት የኾነ ትርጉም ያለው ሀሳብ ስብስብ ነው፡፡
 • ርዕይ በባሕሪው አይቀየርም – አይለዋወጥም፡፡ ምክንያቱም ማዕቀፉ የረዥም ጊዜ ስለኾነ ግብ በአንጻሩ በየጊዜው – በጊዜና በመጠን እንዲሁም በሥራ መለኪያዎች በየጊዜው እየተለዋወጠ ይሄዳል፡፡ ዓላማ እንዳለው ተልዕኮ የሚወሰን መኾኑ ግልጽ ጽንሰ ሀሳባዊ መነሻ ቢኾንም – በሀገራችን ግን ይህን ጽንሰ ሀሳባዊ መሠረት ባልያዘ መልኩ ተቀምጠው ይገኛሉ፡፡
 • ቢያንስ እንˆን እንዴት ርዕይን በማስቀመጥ ከአፍሪቃ መውጣት ያቅተናል? እንዴት አድማሳችን ዓለም አቀፍ መኾን አይችልም? እንዴት ርዕያችን እጅግ የጠበበና ትውልድ የማይሻገር ይኾናል?

– የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባህልና ቱሪዝም

ርዕይ፡ “በኢትዮጵያ በ2012 ዓ.ም ባህላዊ ሀብቶቿና የተፈጥሮ መስህቦቿ ለምተው በቱሪዝም መዳረሻነት ከመጀመሪያዎቹ አምስት የአፍሪካ አገራት አንዷ እንድትሆን ማድረግ፤”

ከላይ የተጠቀሱት አካላት ለምን አድማሳቸው ጠባብ ኾነ? ለምን ግብና ርዕይን መለየት አቃታቸው? ርዕይስ ለነሱ ምንድነው? ዕውን የርዕይ ምንነት ገብ~ቸዋል? በነጠላ የነሱ እንደዚህ መኾን – የአንዳንዶች ደግሞ ከዓለም አቀፍ ጋር ተያይዞ መቅረብና አድማሳቸው ዓለም አቀፋዊ መኾን እንደሀገር በርዕይ ላይ የጠራ ግልጽ የኾነ መግባባት እንደሌለ ማሳያ አይደለምን?

እንደሀገር የርዕይ አልባነትና መደነባበር ውስጥ እንዳለን ከዚህ በላይ ምን ማሳያ ይኖር ይኾን? አንዳንዱ ርዕዩ በአፍሪቃ የታጠረ – የአንዳንዱ ሥራውን ርዕዩ ያደረገ – አንዳንዱ ከሀገሪቱ ‘ርዕይ’ በላይ አንዳንዱ ደሞ በታች ‘ርዕያቸውን’ ያደረጉ መኾናቸው /ከ2015 ዓ.ም በፊትና በኃላ/፤ አንዳንዱ ግቡን ርዕይ ያደረገ – አንዳንዱ ተልዕኮውን ሥራው ያደረገ – – – መኾኑ ሀገራችን ወዴት ነው እየሄደች ያለችው? ምን ርዕይ ይዘን ነው እየተÕዝን ያለነው? እስከ ዛሬ ይህ ክፍተት ለምን አልታየም?

 1. የቅደም ተከተልና ወጥነት ያለው አቀማመጥ አለመኖር፤
 • በርካታ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችም ኾኑ የመንግሥት አካላት ርዕይ – ግብ – ዓላማ – ተልዕኮ – እሴት (deductive መንገድ) አልያም ዕሴት – ተልዕኮ – ዓላማ – ግብ – ርዕይ (inductive መንገድ) በማለት ወጥነት ባለው መልኩ ማስቀመጥ ሲገባቸው እጅግ በተዘበራረቀና ወጥነት በሌለው መልኩ አንዳንዶች ርዕያቸውን ከተልዕኮ በታች ሲያደርጉ፤
 • ለአብነት፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሬ ባህልና ቱሪዝም ተልዕኮን አስቀድሞ ርዕይን ከታች ዕሴትን ከታች በማድረግ ሲገልጽ ሌሎች በአንጻሩ ርዕይን ከላይ ከዚያ ተልዕኮ እንዲሁም ዕሴትን ይገልጻሉ፡፡ በአንዳንዶች እንደገቢዎች ያሉ ደግሞ ስትራቴጂ የሚል ጨምረው ይታያሉ፡፡
 1. ተመጋጋቢነትና ተደራሽነትን ከባለቤትነት ጋር የመያዝ ክፍተት፤
 • ከላይ የተገለጹትም ኾነ ያልተገለጹ ሌሎች አካላት ርዕይ፣ ግብና ተልዕˆቸው ሕዝብ እንደሕዝብ ብቻ ሳይኾን በራሳቸው በመስሪያ ቤቱ ሰራተኞች በራሱ የማይቀነቀን፣ በባለቤትነት ስሜት የማይነሣ ብሎም ብሔራዊ መግባባትን፣ ብሔራዊ መንፈስና ሕዝባዊ መነሣሣትን ያልፈጠረ መኾኑ በአደባባይ የሚታይ ነው፡፡
 • ምናልባትም አካላቶቹ ሕዝባዊ የባለቤትነት ስሜትን መፍጠር ቢችሉ ኖሮ ክፍተቶችን ለማየት የሚያስችላቸው ይኾን አልነበርን? ክፍተቶቹስ አይደሉ ሕዝባዊ የባለቤትነት ስሜትና ብሔራዊ መግባባት እንዳይኖር ያደረጉት?

ክፍተቱም ሕዝብ ራሱም ቢኾን ገዥዎችን ለምንድነው ምትመሩን? የት ለመድረስ? ለምን? ተፎካካሪዎችን ለምንድነው እንድንመርጣችሁ የምትፈልጉት? የት ልታደርሱን? ለምን? ሀገራዊ ርዕይ – ሀገራዊ ግብ የታላችሁ? የፓርቲና የሀገር ርዕይና ግባችሁን ለይታችሁ ንገሩን? የናንተ የፓርቲ የታል? መሪ ብትኾኑስ ለሀገራችን የያዛችሁት የታል? ብሎ ትርጉም ባለው መልኩ አለመጠየቁ፤ ጋዜጠኞችና ምሁራን በዚህ ዙሪያ ሰፊ ሥራ አለመሥራታቸው፤ ክፍተቱ ክፍተት ከመኾን ባሻገር ክፍተቱን እንደክፍተት አለመረዳታችን የኹላችንም የፖለቲካ ንቃተ ህሊና ደረጃ ማሳያ ይመስለኛል፡፡

በርካታ በሀገራችን በተለያዩ ጊዜያት የወጡና ለመተግባር የተሞከሩ – ፖሊሲዎች፣ ፕሮግራሞች፣ ስትራቴጂዎችና ሪፎርሞች በሌሎች ሀገራት ስኬታማ ከመኾናቸውም ባሻገር በጽንሰ ሀሳብ የተVሉ ኾነው ሳለ በሀገራችን ግን የሚፈለገውን ውጤት ሳያመጡ ቀርተዋል፡፡ ይህም ተግባራዊ ሲደረጉ ውጤታማ ካልኾኑባቸው ምክንያቶች አንዱና ዋነኛው ካመጣጣቸው፣ ከአቀራረጻቸው፣ ከአቀራረጽ ሂደታቸው፣ ከትግበራቸው አንጻር ሀገራዊ ማዕቀፍን ትርጉም ባለው መልኩ መነሻና መዳረሻ የማድረግ ብሎም ለሀገራዊ ማዕቀፍ ምሰሶ ከኾኑ ሀገራዊ ርዕይ፣ ሀገራዊ ግብ፣ ሀገራዊ ዓላማና ሀገራዊ ተልዕኮ ጋር ትርጉም ባለው መንገድ አለመተሳሰራቸው ነው፡፡ ስለሆነም ውጤታማ መኾን አልቻልንም፡፡ ልንኾን አለመቻላችን ብዙ አያስገርምም፡፡ ሊያስገርም የሚችለው ውጤታማ ብንኾን ነበር፡፡ ካኹን በኃላም ቢኾን ይህን ክፍተት ካላረምን ጊዜ ያልፋል፤ ሃብት ይባክናል እንጂ መቼም ቢኾን መሠረታዊ ለውጥ አናመጣም፡፡

የቅርብ ጊዜ ጠንካራ ወዳጃችን ቻይና “Achieving rejuvenation is the dream of the Chinese people” ሲኖራት በሌላ በኩል – “The Chinese Dream is a Dream of the Country, the Nation as well as all Chinese individuals” መኾኑን የእንቅስቃሴያቸው መነሻና መዳረሻ አድርገው በኹለንተናዊ መንገድ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡

ስለኾነም what is our Dream of the country, the Nation as well as all Ethiopians individuals? ዕውን አለን? ምን? ለምን? እንደሌለን የታወቀ ነው፡፡ ቢኖረን እያንዳንዱ ዜጋ ባቀነቀነው ነበር፡፡ መጽሐፍ “ርዕይ የሌለው ሕዝብ ይጠፋል” እንዳለ ዜጋ በዜጋነቱ የሚያቀነቅነው ነገር ከሌለ ዜጋነት በራሱ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ቢገባ እንደምን የሚያስደንቅ ይኾናል? ፈጣሪ ሀገራችን ነጻ ፍቃድን የኹሉ ነገር ማዕከል ወደሚያደርግ የዕሳቤ ሂደት ትገባ ዘንድ ይርዳን!

ቸር እንሰንብት!  

ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ (ሸክም የበዛበት ትውልድ፡2009 እና የምሰራቃዊት ኮከብ፡ 2010 መጻሕፍት አዘጋጅ)

Share to friends and family
 •  
 •  
 •  
 •  
 •  
 •  
 •  
 •  
 •  

About Zsunshinetube

Each one of us must take personal responsibility to speak up, stand up and defends for each other regardless of ethnicity, religion or any other.
View all posts by Zsunshinetube →

Leave a Reply