ወያኔ ን ከስልጣን ማስወገድ እንጂ መደራደር መፍትሄ አያመጣም

ወያኔ  በመላው የሃገራችን ክፍል እየተቀጣጠላ ባለው ሕዝባዊ አመፅ ያስደነገጠው መሆኑ ይታወቃል

ወያኔ ተገንጣይ ቡድን በሽፍትነት ዘመናቸው ኢትዮጵያን የማፍረስ ዓላማ አንግበው ሲንቀሳቀሱ ከቆዩ በኋላ በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ የተጠላዉንና እየተዳከመ የመጣዉን ወታደራዊ እምባገነን ሥርዓትን አስወግደው በሃይል ስልጣን ላይ ተቆናጠጡ።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሚያስታውሰው በእንግሊዞችና በአሜሪካኖች ተቀነባብሮ በአቶ ሄርማን ኮሆን አጋፋሪነት (mediation) ከሦስት ብሄራዊ ድርጅቶች (EPLF, TPLF ና OLF) ጋር በ1991 በሎንዶን የተደረገዉ ስብሰባ በዋናነት ፀረ ኢትዮጵያ አንድነት ሃይሎችን ለስልጣን የሚያበቃና ጥቅም የሚያስጠብቅ ሆኖም ግን የኢትዮጵያ ሃገራችን እንድትበታተን የሚያስችል ስትራተጂ የተነደፈበት የኢትዮጵያውያን የጨለማ ቀን ነው።

ለይስሙላም ከነርሱ ዉጪ ማንንም ኢትዮጵያዊ ፖለቲካ ድርጀት፥ የሙያ ማሕበራት፥ የመምህራን ማህበር፥ የሰራተኛ ማህበር፥ የተማሪዎች ማህበር፥ የሃይማኖት መሪዎች፥ አርሶ ኣደሮች፥ የታሪክ ተመራማሪዎች፥ ታዋቂ ግለሰቦችና ያአገር ሽማግሌዎችን ያላሳተፈ የሽግግር መንግሥት አቋቋምን አሉ።

ለነርሱ በሚመችና የታገሉለትን ዓላማ የሚመጥን፥ የሃገሪቱን ዓንድነት የሚንድ፥ የሕዝቡን ለዓላዊነትን የማያከብርና የቋንቋ ፈደራሊዝምን በዋናነት የአገሪቱ የአሰተዳደር ስርዓት እንዲሆን ሕገ-መንግስት አርቅቀው ራሳቸው አፅድቀው የሃገሪቱ ሕገ መንግስት ነው ብለው ሕዝቡ ያልመከረበት፥ያልተሳተፈበት፥ ዕዉንታዉን ያልሰጠበትና፥ ያለዉዴታ በግዴታ ተግባራዊ እንዲሆን አደረጉ።

በመሆኑም ሃገራችን በወያኔ አገዛዝ ሥር ከወደቀችበት ጊዜ ጀምሮ ለብዙሺ ዘማናት ተፈቃቅሮና ተከባብሮ ይኖር የነበረዉን ሕዝብ በብሄርና በቋንቋ በመከፋፈል ሕዝብ እርስ በራሱ እንዲጨራርስ፥አንድነቷንና ህልዉናዋን አደጋ ላይ እንዲወድቅና እንድትበታተን፥ የባህር በር አልባ በማድረግ በኢኮኖሚ የላሸቀች አገር ኣድርጎ ህዝቧን ለረሃብ፥ ለድህነት፥ ለችግርና፥ለስደት ዳረጉት።

ተግራይን እንደ ሃገር ለመመስረት ሊያበቃት የሚችል አስተማማኝ ኢኮኖሚ እንዲኖራት ለማድረግ በታሪክ አንድም ቀን በትግራይ አስተዳደር ሥር ሆነው ያማያውቁትንና የጎንደር አካል የሆኑትን የወልቃይት፤ጠገዴና ጠለምት ለም መሬቶችንና በወሎ የራያን ለም መሬት ወደ ትግራይ እንዲካለል ከማድረጋቸውም ባሻገር የአከባቢው ተወላጆች የሆኑትን የአማራ ማህበረሰብ ላይ ህጻን፤ ሽማግሌ፤ ወንድ ሴት ሳይለዩ በመደብደብ፤ በማሰርና፤ በሰው ልጆች ዘንድ ሊፈፅም የማይገባው ኢሰብዓዊ ድርጊቶችን ከፈፀሙባቸው በኋላ ከተወለዱበት ቀዬአቸው በሃይል ገፍትሮ እንዲሰደዱ በማድረግ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ከትግራይ አምጥተው በማስፈር መሬቱ የትግራውያኖች እንዲሆን አድርገዋል።

የትግራይ ነፃ አውጪ ድርጅት (ህወሃት) በመላው የሃገራችን ክፍል እየተቀጣጠላ ባለው ሕዝባዊ አመፅ ያስደነገጠው ከአሁን ቀደም ይጠቀሙበት የነበረውን ሕዝብንና የዓለም ሕብረተሰብ አታሎ ለማለፍ የሚያስችል ሁለት የአማራጭ መፍትሄዎች በመንደፍ ዳግም የመልሶ ማንሰራራት ዘዴውችን ዕዉን ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ ይሄዉም፦

 1. የትግራይ ሪፐብሊክን ተግባራዊ ለማድረግ በመላው የገጠርና የከተማው አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ሐዝቡን ከኢትዮጵያ ተገንጥለን ራሳችን ብንችል ምን ይመስላችኋል? በማለት የህዝቡን አስተያየት በማሰባሰብ ላይ መሆናቸዉን የተለያዩ ሚዲያዎችና ሶሺያል ሚዲያዎች ዘግበዉታል። ለምን አሁን ለሚለው ጥያቄ መልሱ በመላው የሃገራችን ክፍል በተነሳው ሕዝባዊ አመፅ ምክንያት አገሪቱን መቆጣጠርና ማስተዳደር በማይችሉበት ደረጃ በመድረሱ ይህን የመገንጠል ሃሳብ ህዝቡን በማለማመድ ተግባር ላይ ተጠምደው ይገኛሉ።
 2. የውጭ ደፕሎማቶችን አቅመ ዳካማ ከሆኑት ከተወሰኑት ድርጅቶች ጋር ሰልጣን እጋራለሁ ስለሆነም ከማነኛዉም የፖለቲካ ድርጅት ጋር ለመደራደር ዝግጁ ነኝ በሚል የተለመደው ስልታዊ ተንኮል በመሸረብ ድርጅታቸዉን አጠናክረው የህዝብን የነፃነት ጥያቄ ለመንጠቅ ሥውር ዘምቻ እንደከፈተቱ ታዛቢውች ይናገራሉ።

ይህ ነገር ግን እጅግ ተጠናክሮና ወደፊት ገፍቶ የሚሄድ ከሆነ በጉልበት የወሰድዋቸዉን የጎንደር ክ/ሃገር አካል የሆኑትን የወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ጠለምትና የወሎ ክሃገር እካል የሆኑት የራያ አከባቢዎችን በተመለከተ የተጠየቁት የህዝብ የማንነት ጥያቄዎች አሁኑን መፍትሄ ካልተደረገላቸው ህዝቡ ወደ የማያባራ እልቂት
መግባቱ የማይቀርለት ጉዳይ ነው።

ለተከበርከው የጎንደር ህዝብና የአማራ ብሄረሰብ ባጠቃላይ አንተን የሚወክል የተደራጀና የተጠናከረ ሃይል ባለመኖሩ ለሃያ ስደስት ዓመታት ማንነትህ፥መሬትህና አንጡራ ሃብትህን ተቀምተሃል፥ በሺዎቹ የሚቆጠሩ ዜጎችህን አጥተሃል፥በሚልዮን የሚቆጠሩ ተወልደው ካደጉበት ቀያቸው በማፈናቀል ለስደት ተዳርገዋል። አሁንም ቢሆን እንደ 1991ዓ/ም የተወሰኑ ቡድኖች ይህን እኩይ ለሃገርና ለሕዝብ የማይጠቅም እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው ተብሎ የሚናፈሰው ወሬ እርግጠኛነት ካለው መፃኢው እድልህም ካለፈ የተለየ እንደማይሆን ተገንዝበህ ዳግም እንዳይሰረይብህ በቅርብ ሆነህ መከታተል ይኖርብሃል። ምክንያቱም የጉዳዩ ባለቤትና ወሳኙ እንተ እንጂ ማንም ሊወስንልህ አይችልምና።

በየቅርንጫፉ የተለያየ ሥም በመለጠፍ ውሃ በማይቋጥር ንትርክ እሰጥ አገባ እያልክ ከመነታረኩ ይልቅ ልዩነትህን አጥብበህ አንድ በመሆን የወገንህን ሥቃይ እንድትታደግ፤ በአንተ አያቶችና ቅድመ አያቶች አጥንትና ደም የተገነባችዉን ኢትዮጵያ መልሰህ አንድ የማድረግ ሃገራዊ ሃላፊነትና የታሪክ ግዴታ አለብህ።

ስለዚህ ካለፈው ስህተቶች ትምህርት በመቅሰም ለወደፊቱ እንዳይደገሙ ለማድረግ የሚጠቁሙ ኣስተያየቶችየን እንደሚከተለው አቅርበናል።

የኢትዮጵያ መፃኢ ዕድል የሚወስነው፦

 • መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያሳተፈ ሕገ መንግስት ማርቀቅና ማስፀደቅ
 • ተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጀት፥ የሙያ ማሕበራት፥ የወጣቶች ማህበር፥ የሴቶች ማህበር፥ የስብዓዊ ተሟጋቾች ማህበርን ያሳተፈ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ማድረግ።
 • በተለያዩ ድርጅቶችና ማህበረሰቦች የተወከሉ፥ ተጠሪነታቸውና ውክልናቸው ለመላው ሕዝብ የሆነ ነፃና ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ እንዲቋቋም ማድረግ

የሚሉት ለአንድ ሃገር መሰረታዊ መስፈርቶች በመሆናቸው በተግባር መዋላቸውን ማረጋገጥ መቻል አለበት።

ይህ ሳይሆን ቢቀርና በአንፃሩ የተወሰኑ ድርጅቶችን ብቻ ያሳተፈና ሌላዉን ማህበረሰብ ያገለለ አካል ስልጣን ላይ ሊወጣ ቢያስብ ግን በ1991 ሎንዶን ላይ የተከሰተዉን ክስተት ከመድገም ባሻገር ሃገሪቱ ካለችበት መስቀለኛ መንገድ በከፋ መልኩ ሊቀጥል እንደሚችል በ26 የወያኔ ሃርነት ትግራይ የስልጣን ዘመን ያየነው ሃቅ ነው።

ስለሆነም ሃገራችን ከገባችበት ከባድ ፈተና ማውጣት እንዲቻል ሁሉም ተቃዋሚ ድርጅቶች፥ የሙያ ማህበራት፥የሃይማኖት መሪዎች፥የወጣት ማህበር፥ የሴቶች ማህበር በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚል ዜጋ በሙሉ ልዩነታቸውን በማቻቻል በአድነት በመነሳት ወያኔን ለአንዴና ለመጨረሻ ለማስወገድ ይቻል ዘንድ ጥሪ እናቀርባለን።

በመጨረሻም በኤሊባቡር መቱ፥ በአምቦ፥ በጫንጮ፥ በጉደር፥ በፊቼ፥ በኢትዮጵያ ሶማሊዎችና በኦሮሞ ማሕበረሰብ፥ቤኒሻንጉል በሚኖሩ የዓማራ ብሄረሰብ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን ላይ የደረሰዉንና እየደረሰ ያለዉን የጅምላ ግድያ፥ ጭፍጨፋና ሰቆቋ እያወገዝን ዛሬም፥ ነገም ከነገ ወድያም የትግላችሁ አካል መሆናችንን ልናረጋግጥላችሁ እንወዳልን።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ለዘልዓለም በክብር ትኑር!

የኦሮሞ ሕዝብ ደም የኢትዮጵያውያን ደም ነው!!

ልሳነ ግፉዓን የወልቃይት ጠገዴና የጠለምት ማንነት ጥምረት ጊዜያዊ ኮሚቴ

Share to friends and family
 •  
 •  
 •  
 •  
 •  
 •  
 •  
 •  
 •  

Leave a Reply