ከስፖርት መዓድ- አጫጭር የውጪ ስፖርታዊ መረጃዎች – ጁሊየት ተድላ አስፋው 

ከስፖርት መዓድ

ከስፖርት መዓድ – የአርሰናሉ አሰልጣኝ አርሰን ቬንገር ኦክስድ ቻምበርሊንን ለምን ለመሸጥ ውሳኔ ላይ እንደደረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ አብራርተዋል፡፡

 • እንደ ሳንቼዝና ኦዚል ሁሉ የአንድ ዓመት ቀሪ ኮንትራት በመድፈኞቹ ቤት ይቀረው የነበረውን እንግሊዛዊ ተጫዋች በ35 ሚሊየን ፓውንድ ለሊቭርፑል አሳለፈው የሰጡት ኢኮኖሚስቱ ’’ኮንትራቱን እንዲያራዝም እንፈልግ ነበር፡፡ ነገር ግን ሊጁ ፍቃደኛ አልነበረም፡፡ ክለቡን መልቀቅ ይፈልግ ነበር፡፡ ውሳኔውን ልናከብር ችለናል፡፡’’ ሲሉ ምክንያታቸውን ለመስጠት ሞክረዋል፡፡

ነገር ግን ኦዚል እና ሳንቼዝም እንደ ቻመበርሊን ሁሉ ቀሪ አንድ ዓመት ኮንትራት የቀራቸው የነበረ ቢሆንም ቬንገር ግን ተጫዋቾቹን ለመልቀቅ ፍቃደኛ አለመሆናቸው ይታወሳል፡፡

 • የኤቨርተኑ እንግሊዛዊ ተጫዋች ሮስ ባርክሌይ ባለፈው የዝውውር መስኮት ቼልሲን ለመቀላቀል ከጫፍ ደርሶ ባልታወቀ ምክንያት ዝውውሩ ሳይሳካ መቅረቱ ይታወቃል፡፡

አሁንም ግን በጥር የዝውውር መስኮት ኤቨርተንን እንደሚለቅ የሚታመነው ባርክሌይ ቶትንሀም እና ቼልሲ ተጫወቹን የማግኘት ዕድል ተሰጥቷቸዋል፡፡

በኤቨርተን የመቆየት ፍላጎት የሌለው የ24ዓመቱ እንግሊዛዊ ቀጣይ እጣ ፈንታው በእጁ እንደሆነ በቅርቡ የመርሲሳይዱን ክለብ በአሰልጣኝነት የተረከቡት ሳሚ አላርዳይዝ ገልፀዋል፡፡ባርክሌይ በአሁን ሰዓት በጉዳት ላይ የሚገኝ ሲሆን በአዲሱ ዓመት ግን ወደ ሜዳ ይመለሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 • የቼልሲው ተከላካይ ዴቪድ ሊዊስ አሁን ባለው ሁኔታ በሰማያዊዎቹ ቤት የተረጋጋ አይመስልም፡፡ አንቶኒዮ ኮንቴም በተጫዋቹ ላይ ያላቸው ዕምነት የቀነሰ ይመስላል፡፡

የተጫዋቹ ስም ከሪያል ማድሪድና ከአርሰናል ጋር እየተያያዘ ቢገኝም አሁን ደግሞ የውሰት ጥያቄ በመያዝ የቼልሲዎችን በር ያንኳኳው ባርሴሎና ብራዚላዊውን የማግኘት ዕድል ተሰጥቶታል፡፡

በወጣቱ አንድርስ ክሪስትስተን ከጉዳት መልስ ቦታውን የተነጠቀው ሊዊስ የአለም ዋንጫ ተሳትፎውን ለማረጋገጥ ሲል ቋሚ ተሰላፊ ወደ ሚሆንበት ክለብ ማምራቱ አይቀርም እየተባለ ይገኛል፡፡ እናም በቀጣይነት ሊዊስ በማድሪድ፣ በአርሰናል አሊያም ደግሞ በባርሴሎና ማልያ ሊታይ ይችላል ማለት ነው፡፡

 • ማንቸስተር ዩናይትድ በብሪስቶል ሲቲ 2 ለ1 በመሸነፍ ምክንያት ከተተቹ ተጫዋቾች መካከል ማቲው ዳርሜይን ይገኝበታል፡፡

ጣሊያናዊው ተጫዋች የአንቶኒዮ ቫሌኝሽያ ተጠባባቂ በመሆን ዩናይትድን እያገለገለ ሲሆን በዚህ የውድደር ዓመትም በ10 ጨዋታዎች ብቻ ነው መሰለፍ የቻለው፡፡ ይህን ተከትሎም ወደ ሴሪአ ይመለሳል የሚሉ ዘገባዎች እየተበራከቱ ናቸው፡፡

በ2015 ከቶሪኖ ዩናይትድን የተቀላቀለው ዳርሜይንን ለማዘዋወር ጁቬንቱስ፣ ናፖሊና ሮማ ፍላጎት ያሳዩ የጣሊያን ክለቦች ናቸው፡፡

 • ብራዚላዊው ኔይማር 200 ሚሊየን ፓውንድ ወጥቶበት ወደ ፒኤስጂ መዘዋወሩ ይታወሳል፡፡ ሆኖም ግን ተጫዋቹ የፈረንሳይን የአኗኗር ዘይቤ መላመድ አልተቻለውም የሚሉ ዘገባዎች በተደጋጋሚ እየወጡ ይገኛሉ፡፡

ይህን ተከትሎም ወደ ሪያል ማድሪድ ያቀናል የሚሉ ወሬዎች ሲናፈሱ ቖይተዋል፡፡ ሆኖም ግን የፒኤስጂ ፕሬዝደንት ናስር አል ኬላፊ ወሬውን ’የማይቻል እና የማይሆን ሲሉ አጣጥለውታል፡፡ነገር ግን ማድሪዶች ከተወሰነ ዓመት በኋላም ቢሆን ብራዚላዊውን ማግኘታቸው አይቀርም የሚለው ሀሳብ የብዙዎች ሆኗል፡፡

Share to friends and family
 • 3
 •  
 •  
 •  
 •  
 •  
 •  
 •  
 •  
  3
  Shares

Leave a Reply